ራስብሩ ወልደገብርዔል ትምህርት ቤት

ንም ሠው የተወለደበትን ያደገበትን እና ፊደል ቆጥሮ የተማረበትን አካባቢ ከምንም በላይ ይወዳል በህይወት ዘመኑም ሁሉ ያስታውሰዋል :: ራስብሩ ወልደገብርኤል ትምህርት ቤት ከተመሠረተ ከ1944 ዓ.ምህረት ጀምሮ ከዚህችው ትምህርት ቤት ፊደል ቆጥረው ያደጉና እጅግ ከፍ ያለ ደረጃ የደረሱ ተማሪዎች ቁጥራቸው ቀላል አይደለም:: ከዚያ በፊት ቀደም ብሎ የነበረው በክብረመንግሥት የመጀመሪያው ትምህርት ቤት ኩሚና ትምህርት ቤት ይባል የነበረው ሲሆን አሁን ድረስ ስሙና ቦታው ያለ ቢሆንም ከአንደኛ ደረጃ ከፍ ብሎ አያውቅም:: ኩሚና ትምህርት ቤት በሺህ ዘጠኝ መቶ ሠላሳዎቹ እንደተጀመረ አንዳንድ የታሪክ መረጃዎች ያስረዳሉ:: ይሁን እንጂ ከዚያም ቀደም ብሎ አለቃ ደሳለኝ የሚባሉ መምህር ተማሪዎችን እየሰበሰቡ በኍላ ኩሚና ትምህርት ቤት የተሰራበት ቦታ ላይ ያስተምሩ እንደነበር ይነገራል:: የኩሚና ትምህርት ቤት የነበረው ደረጃ እስከ ስድስተኛ ክፍል ድረስ ብቻ ነበር::

በወቅቱ የሁለተኛ ደረጃን ትምህርት ለመማር አንደኛ ደረጃን ያጠናቀቁ ተማሪዎች ሀይስኩልን ለመቀጠል በይርጋዓለም ራስ ደስታ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሄደው መማር አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነበር:: በዚህም መሠረት ስድስተኛን ያጠናቀቁ የመጀመሪያዎቹ ምሩቆች (ተማሪዎች) የሰባተኛና የስምንተኛ ክፍል ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉ ወደ ይርጋዓለም ራስ ደስታ ትምህርት ቤት ተላኩ:: ነገር ግን በቤት ኪራይ በምግብ በትምህርት መሣሪያዎች እንዲሁም በተለያዩ የኪስ ገንዘብ ወጪ ማሟላት ስለቸገራቸው ከአንድ አመት በላይ ቀጥለው መማር አልቻሉም በዚህም ምክንያት ትምህርታቸውን ጥለው ለመመለስ ተገደዋል። ከዚያ በኋላ 6ኛ ክፍል የደረሱት ተማሪዎች ሁሉ ወይ እዚያው ያንኑ ክፍል ሳይወዱ መድገምና መማር ወይም ደግሞ መማር ካልፈለጉ ሥራ ፈልገው መሄድ ይገደዱ ነበር:: በዚህም የተነሳ የአዲሱን ትምህርት ቤት መከፈት በጉጉት የማይጠባበቅ አልነበረም።

የኩሚና አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በዘመናዊው የራስ ብሩ ወልደገብርኤል ሲተካ የመጨረሻው የትምህርት ቤቱ ዳይሬክተር የነበሩት አቶ ንዋይ ወልደማሪያም ናቸው:: በራስብሩ ወልደገብርኤል ስም መንግሥት ያስገነባው ትምህርት ቤት ዘመናዊና የተሟላ የላብራቶሪና የቤተመጻህፍት አገልግሎት ከመስጠቱም በላይ ደረጃው ከአንደኛ እስከስምንተኛ ክፍል ድረስ መማር የሚያስችል ነበር:: ይህንን ትምህርት ቤት ራስብሩ ወልደገብርኤል እንዳስገነቡት የመጀመሪያው የትምህርት ቤቱ ዳይሬክተር የህንድ ዜጋ የሆኑ ሚስተር ዘካሪያስ የሚባሉ ሰው ነበሩ:: እኚህ ሰው እንግሊዝኛ ታሪክና ጂኦግራፊ ሲያስተምሩ ባለቤታቸው ሚስስ ዘካሪያስ ደሞ የሳይንስና የማተማቲክስ መምህር ነበሩ::

እኚህ ህንዳዊ መምህር በነበሩበትና ትምህርትቤቱን ባስተዳደሩበትም ወቅት ብዙ መልካም ነገሮችን ሠርተው እንደነበር በእሳቸው ዘመን የነበሩ ተማሪዎች አሁን ድረስ ያስታውሳሉ:: ለምሳሌ ያህል የመጀመሪያው የራስብሩ ተማሪዎች ቦይስካውት የተመሰረተው በሳቸው ዘመን ነው:: የቦይ ስካውት አባላት የውሀ ዋና ማወቅ ስለነበረባቸው አንፈራራ አካባቢ አንድ ሰፋ ያለ የመዋኛ ሥፍራ ተዘጋጅቶ የራስብሩ ቦይ ስካውቶች ይለማመዱበትና ይዋኙበት እንደነበረ በወቅቱ የነበሩት ልጆች ያስታውሳሉ:: እንዲሁም ተማሪዎች ድራማና ቴያትር እያዘጋጁ የከተማይቱን ስዎች እየጋበዙ ያስተናግዱ ነበር።  የእግር ኳስና ቮሊቦል (የመረብ ኳስ) ሰፖርት ይበልጥ የተስፋፋው በዚያን ጊዜ ነበር።

የራስ ብሩ ወልደ ገብርኤል ትምህርት ቤት መጀመሪያ ሲከፈት እስከ ሰባተኛ ክፍል ድረስ ብቻ ነበር ለዚህም ምክንያቱ የኩሚና ትምህርት ቤት የመጨረሻው ከፍተኛ ክፍል እስከ 6ኛ ብቻ ስለነበር ቢሆን ከሁለት ዓመት በኍላ በ1946 ዓም. እስከስምንተኛ ክፍል የማስተማር አቅም እንዲኖረው ተደረገ:: በዚያው የትምህርት ዓመት የመጀመሪያዎቹ የአዶላ ልጆች የሚኒሰትሪን ፈተና ለመጀመሪያ ግዜ ተቀበሉ ፈተናውን ከተቀበሉትም ውስጥ አንድም ተማሪ ሳይወድቅ ሁሉም በማለፋቸው ለከተማዪቱም ሆነ ለነዋሪዎቹ ትልቅ ኩራትና ደስታ ሆነ:: ከዚያም ተመራቂዎቹ አዲስ አበባ ሄደው በተለያዩ አዳሪ ትምህርት ቤቶች የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉ ተደረገ:: በወቅቱ ከነበሩትና የመጀመሪያዎቹ የስምንተኛ ክፍል ተመራቂዎችም የሚከተሉት ነበሩ::

እነዚህ ሁሉም ወደ አዲስ አበባ ተልከው በተለያዩ 2ኛ ደረጃ ት/ቤቶች በአዳሪነት እየተማሩ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል:: ኃይለ ሚካኤል ቦረዳ ፣ ቃሉ ጉደታና ምሥጢር ዓየለ ኮተቤ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሲላኩ ። የዳይሬክተሩ ልጅ ህንዳዊው ኮሺ ወደሀገሩ ተላከ:: ደምሴ ዓለሙ ተግባረ ዕድ ትምህርት ቤት ፣ ዮሐንስ ገብሬ ንግድ ሥራ ት/ቤት : ተስፋየ ደጋጋና በቀለ ሙለታ፣ በእድሜም ትላልቆች ስለነበሩ፣ የአንድ ዓመት ኮርስ እንዲከታተሉ፣ ቀበና ወደሚገኘው ቀ.ኃ.ሥ. መምህራን ማሰልጠኛ ት/ቤት ተመድበው ትምህርታቸውን በሚገባ ተከታትለዋል:: ከእነዚህ መካከል ጥቂቶቹ ከዚህች ዓለም በሞት ሲሰናበቱ ኃይለ ሚካኤል በረዳ : ዮሐንስ ገብሬ : ቃሉ ጉደታና : ምሥጢር ዓየለ በተለያዩ የሥራና የኑሮ ሁኔታ ላይ በህይወት ይገኛሉ:: ፕሮፌሠር ኃይለሚካኤል በረዳ (ተመራማሪ ሳይንቲስት) በመሆን በትምህርት የላቀ ደረጃ ላይ ደርሷል ::

ይህንን ታሪክ ያገኘሁት ይድረስ ለራስብሩ ወልደገብርዔል ልጆች ከሚለው ከዋርካ አምድ ሥር ሲሆን ትልቁን የታሪክ ምንጭ አንፈራራን እንዲሁም ሽልንግዬን እና አደቆርሳን ግን ከልብ ላመሰግን እወዳለሁ::
Rasbru Woldegebriel.

Some related Articles