ስደት

ጉም ሠማይን ንቆ

ምድር ወርዶ ተደብቆ

እንዳይታይ ካድማስ ርቆ

እንዳይነጋ ተጠንቅቆ

ለጽድቅ የጠሩት ለመከራ

ሆነና የዘመኑ ተራ

ያዲስ ዘመን አዲስ ቅኔ

በግድ አምጥቶ ኩነኔ

ባይካፈል ቁርሱን

ባይጠጣው ድግሱን

የተመኘው የሞተለት

 የጥፋት ድር ሲያበጅለት

ውሎ መግባት ህልም ሲሆን

ተስፋ እንደጉም ሲበን

የጮኸለት አብዮቱ ፊቱን ዞሮ ሲጮሀበት

በራሱድል በራሱቀን የጭቃ ሹም ሲሾምበት

ባውራ መንገድ ባደባባይ የግፍ ስቃይ ሲደርስበት

ከወላጅ ጉያ ሲነጠቅ እንደጭዳ በግ ሲበለት

በቃኝ አለ ያ ወጣት

በቃኝ .... ፍትህ አልባ ህይወት !

በሰማየ ሠማያት ሀሩር

ምድር በሚነድበት ቀትር

በዶሎ በረሐ እሳት ...............  ቀን ከሌሊት ሳይበገር

ደራሽ ውሃ ሳያሰፈራው...........  በጥሾ ጀልባ ሲሻገር

በርሀብ አንጀቱን ርቆ

በጥማት ከንፈሩ ደርቆ

በሥጋት ልቦና ነፍስ ከስጋ ተላቆ

የነገን ብሩህ ህይወት በመንፈስ ተስፋ ሠንቆ

የወጋው እሾህ ሳይነቀል ዳግመኛ በሾህ ተወግቶ

ረሃብ ድካምን አግዞ ወኔ ጉልበትን አጥቶ

እመ ብርሃን ድረሺልኝ በጸሎት ተስፋ ተሞልቶ

ድንበሩን ጣሰ ያ ወጣት ሄደ ሀገሩን ትቶ

ነጌኛ ሰፊያተኡ ያ አዶላ ኮ

ነጌኛ ሰፊያተኡ ያ ወዩ ኮ

እናት አባቱን ተወ በፍትህ ፍቅር ተማርኮ

1969 ዓ.ምህረት

 

መታሠቢያነቱ በጸረ ወታደራዊ አገዛዝ ትግል ከሀገር  ለተሰደዱት የክብረመንግሥት ልጆች ይሁንልኝ

ክብረመንግሥት